AM/Prabhupada 1072 - ይህንን የቁሳዊው ዓለምን ትተን ወደ ዘለዓለማዊው ሕይወት እና ወደ ዘለዓለማዊው ቤተ መንግስት መሄድ ይገባናል፡፡



660219-20 - Lecture BG Introduction - New York

ዓብዩ ጌታም በቸርነቱ “ሽያማሱንዳራ” ተብሎ በሚታወቀው ፎርሙ ይቀርብልናል፡፡ ቅር የሚያሰኘው ግን አንዳንድ ዝቅተኛ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች እንደሰው ተመስሎ ሲወርድ በንቀት ዓይን ያዩታል፡፡ “አቫጃናንቲ ማም ሙድሀ” (ብጊ፡ 9.11) ይህም ምክንያቱ ዓብዩ ጌታ ልክ እንደ እኛ የሰው ልጅን ተመስሎ በመምጣት እና በምድር ላይ በጨዋታ ላይ በመቅረቡ ነው፡፡ ስለዚህ ዓብዩ ጌታ ወደ ምድር ሲወርድ ልክ እንደ እኛ ሰው ነው በማለት ለማሰብ አንችልም፡፡ ዋነኛውን የእራሱን ፎርምንም ይዞ መቅረቡ በኋያልነቱ እና በቸርነቱ ነው፡፡ በምድር ላይ የሚያደርገውም ድርጊት ሁሉ ልክ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ እንደሚያደርገው ድርጊት ነው፡፡ ብራህማ ጆይቲ ተብሎ በሚታወቀውም የመንፈሳዊው ዓለም ሰማይ ውስጥ በቁጥር ሊተመኑ ያማይችሉ መንፈሳዊ ፕላኔቶች አሉ፡፡ ይህም ሊመሰል የሚችለው ልክ በፀሀይ ጮራ ውስጥ ብዙ ፕላኔቶች እንደሚገኙት ነው፡፡ እንደዚህም ሁሉ በብራህማ ጆይቲ ውስጥም ይገኛሉ፡፡ ይህም ብራህማ ጆይቲ የሚመነጨው ክርሽና ሎካ ወይንም ጐሎካ ፕላኔት ውስጥ ከሚገኘው ከዓብዩ ጌታ የገላ ጮራ ነው፡፡ “አናንዳ ቺንማያ ራሳ ፕራቲብሀ ቪታብሂስ” (ብሰ 5 37) እነዚህም ፕላኔቶች ሁሉ የመንፈሳዊ ፕላኔቶች ናቸው፡፡ “አናንዳ ቺንማያ“ ተብለውም የሚታወቁ ናቸው፡፡ እነዚህ ፕላኔቶች ቁሳዊ ፕላኔቶች ሳይሆኑ መንፈሳዊ ፕላኔቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም ዓብዩ ጌታ እንዲህ ይላል ”ና ታድ ብሀሳያቴ ሱርዮ ና ሻሻንኮ ና ፓቫካሀ“ ”ያድ ጋትቫ ና ኒቫርታንቴ ታድ ድሀማ ፓራማም ማማ“ (ብጊ፡ 15.6)

ወደ እዚህም መንፈሳዊ ሰማይ ለመድረስ እድል ያገኘ ሁሉ ወደ እዚህ ቁሳዊው ዓለም እንደገና ተመልሶ ሊመጣ አይችልም፡፡ በዚህ ቁሳዊ ዓለም እስከ አለን ድረስ ወደ ጨረቃ እንኳን በመሄድ ደስታን አናገኝም እንደምናውቀው ጨረቃ ለምድር በጣም ቅርብ ናት፡፡ ቢሆንም ግን ምንም እንኳን ወደ ከፍተኛውን ፕላኔት እንኳን ለመሄድ ብንችል ይህም ”ብራህማ ሎካ“ ተብሎ የሚታወቀው ፕላኔት ዞሮ ዞሮ ሁሉም የቁሳዊው ዓለም ፕላኔቶች መከራ የተሞላባቸው ናቸው፡፡ ይህም ማለት የመወለድ፣ የመሞት፣ የማርጀት፣ እና የመታመም ችግሮች ማለት ነው፡፡ በቁሳዊው ዓለም ውስጥ የሚገኙ ማናቸውም ዓይነት ፕላኔቶች ከእነዚህ ከአራቱ የመከራ ዓይነቶች የራቁ አይደሉም፡፡ ሰለዚህም ዓብዩ ጌታ በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ እንዲህ ብሎ ተናግሯል፡፡ ”አብራህማ ብሁቫና ሎካ ፑናር አቫርቲኖ አርጁና“ (ብጊ፡ 8.16) እያንዳንዱ ነፍሳት ሁሌ ከአንዱ ፕላኔት ወደ ሌላው በመዘዋወር ላይ ይገኛሉ፡፡ በሜካኒካል ስልጣኔ ስፑትኒክ በመፍጠር በቀላሉ ወደ ሌሎች ፕላኔቶች ለመሄድ አይቻልም፡፡ ወደ ሌላ ፕላኔቶች ለመሄድ የሚፈልግ ሰው ሁሉ የተፈጥሮን ስርዓት መከተል ያስፈልገዋል፡፡ "ያንቲ ዴቫ ቭራታ ድቫን ፒትርን ያንቲ ፒትር ቭራታሀ” (ብጊ፡ 9.25) አንድ ሰው ጨረቃን የመሰለ ወይንም ወደ ሌላ ፕላኔቶች ለመሄድ የፈለገ ሁሉ የሜካኒካል ስፑትኒክን ፈጥሮ ለመሄ መጣር አያስፈልገውም፡፡ ብሀገቨድ ጊታም እንደሚያዘን ”ያንቲ ዴቫ ቭራታ ድቫን“ እነዚህ የጨረቃ ፕላኔቶች፣ የፀሀይ ፕላኔት ወይንም ይህ ”ብሁ ሎካ“ ተብሎ ከሚታወቀው ሰማይ በላይ የሚገኙ ፕላኔቶች ሁሉ ”ስቫርጋ ሎካ“ ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ”ስቫርጋ ሎካ“ በዚህ ቁሳዊው ዓለም ውስጥ ሶስት ዓይነት የተለያዩ የፕላኔቶች ደረጃዎች አሉ፡፡ ”ብሁ ሎካ፣ ብሁሁቫር ሎካ፣ ስቫርጋ ሎካ“ ”ዴቫ ሎካ“ እንዲህም ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ብሀገቨድ ጊታም እንዴት ወደ እነዚህ ዴቫ ሎካ ተብለው የሚታወቁ ከፍተኛ ፕላኔቶች በቀላሉ ለመሄድ እንደምንችል ስርዓቱን አቅርቦልናል፡፡ ”ያንቲ ዴቫ ቭራታ ዴቫን፣ ያንቲ ዴቫ ቭራታ ዴቫን“ ”ዴቫ ቭራታ“ ይህም የተመኘነውን መላእክት በማምለክ ነው፡፡ በዚህም መንገድ ወደተመኘነው ፕላኔት ለመሄድ እንችላለን፡፡ እንደፍላጎታችንም ወደ ፀሀይ ፕላኔት፣ ወደ ጨረቃ ፕላኔት ወይንም ወደ ገነት መሄድ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ብሀገቨድ ጊታ ወደ እነዚህ ቁሳዊ ዓለም ፕላኔቶች እንድንሄድ አይመክረንም፡፡ ምክንያቱም ምንም እንኳን ወደ ከፍተኛው ወደ “ብራህማ ሎካ” እንኳን ብንሄድም ከቁሳዊ ዓለም መከራ ልንርቅ አንችልም፡፡ “ብራህማ ሎካ” ወደ ተባለው ከፍተኛው ፕላኔት በዘመናዊ የሳይንቲስቶች ሜካኒካል ስፑትኒክ ለመሄድ በርቀቱ ምክንያት እስከ 40,000 ዓመታት ሊፈጅብን ይችላል፡፡ በዚህም እድሜያችን እስከ 40,000 ዓመታት ለመኖር እና ወደ እዚህ ከፍተኛው ፕላኔት ለመሄድ አንችልም፡፡ ቢሆንም ግን አንድ ሰው በዚህ ፕላኔት ውስጥ የሚገኘውን መልዓክ ቢያመልክ ወደ መልዓኩ ፕላኔት በቀላሉ ለመሄድ ይችላል፡፡ ይህም በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ተገልጿል፡፡ “ያንቲ ዴቫ ቭራታ ዴቫን ፒትርን ያንቲ ፕትር ቭራታሀ” (ብጊ፡ 9.25) እንደዚሁም ሁሉ “ፒትር ሎካ” ተብሎ የሚታወቅ ፕላኔት አለ፡፡ እንደዚህም ሁሉ አንድ ሰው ወደ ዓብዩ ጌታ ፕላኔትም ለመሄድ ከፈለገ ለመሄድ ይችላል፡፡ ይህም የዓብዩ ጌታ ፕላኔት “ክርሽና ሎካ” ተብሎ ይታወቃል፡፡ በዚህም በመንፈሳዊ ዓለም ውስጥ በቁጥር የማይተመኑ መንፈሳዊ ፕላኔቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ዘለዓለማዊ ፕላኔቶች ናቸው፡፡ ለዘልዓለም የማይጠፉ እና የማይደመሰሱ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ መንፈሳዊ ፕላኔቶች መሀከል አንድ ልዩ ፕላኔት አለ፡፡ ይህም ቀዳማዊው እና የበላዩ ፕላኔት “ጐሎካ ቭርንዳቫን” ተብሎ ይታወቃል፡፡ እነዚህም ሁሉ መረጃዎች በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ቀርበውልናል፡፡ የመረዳትም ዕድሉ ተሰጥቶናል፡፡ ይህም እንዴት ይህንን የቁሳዊ ዓለም ትተን እንደምንሄድ እና እንዴት ዘለዓለማዊውን ሕይወታችንንን በመንፈሳዊው ቤተ መንግስት ውስጥ መልሰን እንደምናገኘው ነው፡፡