AM/Prabhupada 1068 - በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ እንደተጠቀሰው በሶስት አይነት ባህርያት የተከፈሉ የተፈጥሮ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡

Revision as of 13:11, 8 June 2018 by Vanibot (talk | contribs) (Vanibot #0019: LinkReviser - Revised links and redirected them to the de facto address when redirect exists)
(diff) ← Older revision | Latest revision (diff) | Newer revision → (diff)


660219-20 - Lecture BG Introduction - New York

አብዩ የመላእክት ጌታም "ፑርናም" ወይንም እንከን የለሽ እና የተሟላ እንደመሆኑ በቁሳዊው ዓለም ህግጋቶች ሊጠቃ የሚችል አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህንን በመረዳት ከአብዩ ጌታ በስተቀር ማንም ሰው በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ጌታ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህም በብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መጽሀፍ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡"አሀም ሳርቫስያ ፕራብሀቮ ማታህ ሳርቫም ፕራቫርታቴ" "ኢቲማትቫ ብሀጃንቴ ማም ቡድሀ ብሀቫ ሳማንቪታሀ" (ብጊ 10.8) ዓብዩ የመላእክት ጌታ ቀዳማዊው ፈጣሪ ነው፡፡ የመጀመሪያው ፍጥረት "የጌታ ብራህማ" ፈጣሪም እርሱው ነው፡፡ ይህም በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ዓብዩ ጌታ "የጌታ ብራህማ" ፈጣሪ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በ11ኛው የብሀገቨድ ጊታም ምዕራፍ ውስጥ ዓብዩ ጌታ "ፕራፒታማሀ" ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ (BG 11.39)(ብጊ 11 39) ምክንያቱም ብራህማ "ፒታ መሀ" ተብሎ ስለተጠራ ነው፡፡ ይህም አያት ማለት ነው፡፡ ዓብዩ ጌታም የአያቱ ፈጣሪ ወይንም "ፕራፒታመሀ" ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው ቢሆን የምንም ንብረት ጌታ ነኝ ለማለት አይገባውም፡፡ ቢሆንም ግን በዓብዩ ጌታ እንደ ራሽን የተመደበለትን ንብረት በመቀበል መንከባከብ ይገባዋል፡፡ ስለዚህም እንዴት የተመደበልንን ለመንከባከብ እንደሚገባን የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎች አሉ፡፡ ይህም በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ተገልጾልናል፡፡ ለምሳሌ አርጁና በመጀመሪያ ደረጃ በጦርነቱ ላይ አልዋጋም ብሎ ወስኖ ነበረ፡፡ ይህም የእራሱ ሀሳብ እና ውሳኔ ነበረ፡፡ አርጁናም እንደገለፀው ከሆነ የራሱን ዘመዶች እና ቤተሰቦች በጦርነት ከገደለ በኋላ የነገስታቱ መሪ በመሆን ሊደሰት እንደማይችል ገልጾ ነበረ፡፡ ይህንንም አስተሳሰብ ይዞ የነበረው እራሱን ከቁሳዊው ገላ ጋር ከሚገናኙት ዘመዶቹ ጋር አስተሳስሮ አስቦ ስለነበረ ነው፡፡ ቁሳዊው ገላውን እንደ ራሱ አድርጐ በስህተት ያስብም ስለነበረ ነው፡፡ ከዚህም ከቁሳዊው ገላ አንፃር ዘመዶቹን ወንድሞቼ የአጐት ያክስት ልጆቼ አማቾቼ አያቶቼ እያለ ያስብ ስለነበረ ነው፡፡ እነዚህም ሁሉ ከቁሳዊ ገላው ጋር የተዛመዱ ናቸው፡፡ ስለዚህም ከዚህ ከቁሳዊው ገላ ጋር የተዛመዱትን የስሜታዊ ፍላጐቶቹን ለሟሟላት ፈለገ፡፡ የብሀገቨድ ጊታም መላ መልእክት በዓብዩ ጌታ የተላለፈው ይህንን የተሳሳተ አስተሳሰቡን ለመቀየር ነበረ፡፡ አርጁናም በዓብዩ ጌታ ስር ሆኖ በመታዛዝ ለጦርነቱ ዝግጁ ለመሆን በቃ፡፡ እንዲህም አለ “ካሪስዬ ቫቻናም ታቫ” (ብጊ 18.73)

ስለዚህ በዚህ ዓለም ላይ የሰው ልጅ እንደ ድመቶች እና እንደ ውሾች የኔ የኔ በማለት መዋጋት እና መበጣበጥ አይገባውም፡፡ የሰው ልጅ ሕይወት አብይ አስፈላጊነትን በመረዳት አዋቂ ሰው መሆን ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም በመረዳት እንደ እንስሳ ከመኖር መቆጠብ ይኖርብናል፡፡ የሰው ልጅ ሕይወት ዓላማም ምን እንደሆነ በትክክል መረዳት ይገባናል፡፡ ይህም መመሪያ በመላ የቬዲክ ስነፅሁፎች ውስጥ ሁሉ ተገልጾልናል፡፡ ጥርት ያለው መልእክትም በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ተገልጾልናል፡፡ የቬዲክ ስነፅሁፎች የቀረቡት ለሰው ልጅ ፍጥረት እንጂ ለውሾች እና ለድመቶች አይደለም፡፡ ድመቶች እና ውሾች ለምግባቸው የሚሆኑትን እንስሶች ገድለው መብላት ይችላሉ፡፡ በዚህም ድርጊት ምንም ዓይነት ሀጥያት ውስጥ ሊገቡ አይችሉም፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ ሊቆጣጠረው የማይችለውን ስሜቱን ለማስደሰት ብሎ እንስሶችን ቢገል የተፈጥሮን ሕግ ስላላከበረ እና ስለሰበረ ሀላፊነቱን ይወስዳል፡፡ በብሀገቨድ ጊታም ውስጥ ሶስት ዓይነት እንቅስቃሴ ወይንም ስራዎች ተገልፀዋል፡፡ እነዚህም በተፈጥሮ ይዘን የመጣናቸው የተለያዩ ባህርዮች ናቸው፡፡ 1. ጥሩ የመስራት ባህርይ 2. ፋታ የለሽ እንቃስቃሴ ውስጥ መሰማራት 3. ድንቁርና የተሞላበት እንቅስቃሴ ውስጥ መሰማራት እንደዚሁም ሁሉ ሶስት ዓይነት ምግቦች ይገኛሉ፡፡ ጥሩ የሆኑ ምግቦች፣ ወደ ፋታ የማይሰጥ እንቃስቃሴ የሚገፋፉ ምግቦች እና በድንቁርና የተሞሉ ምግቦች ናቸው፡፡ እነዚህም ሁሉ በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ በግልፅ ተተንትነዋል፡፡ ይህንንም መልእክት በጥሞና ብንከታተል መላ ሕይወታችን የተሳካ እና ንፅህና የተሞላበት ይሆናል፡፡ በመጨረሻም ወደ ትክክለኛው መድረሻችን እንደርሳለን፡፡ “ያድ ጋትቫ ና ኒቫትታንቴ ታድ ድሀማ ፓራማም ማማ” (ብጊ 15.6)

ይህም መረጃ በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ቀርቦልናል፡፡ ይህም ማለት “ከዚህ ከምናየው የቁሳዊ ዓለም ባሻገር ሌላ ሳናታና ወይንም ዘለዓለማዊ ተብሎ የሚታወቅ መንፈሳዊ ሰማይ አለ” በዚህ በቁሳዊው ዓለም ሰማይ ግን ሁሉም ነገር ጊዝያዊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ማለት ቁሳዊው ዓለም በመጀመሪያው ይፈጠራል፣ ከዚያም ለጥቂት ግዜ ይቆያል፣ ይባዛል ወይንም ይዋለዳል ከዚያም ማርጀት ይጀምራል፣ ከዚያም ይጠፋል፡፡ የቁሳዊው ዓለም ህግጋት ይህ ነው፡፡ ለምሳሌ ይህንን ገላ ውሰዱ፡፡ ወይንም አንድ ፍራፍሬን ውሰዱ፡፡ ይህም አንድ ግዜ ተፈጥሮ በመጨራሻ ግን የሚጠፋበት ግዜ አለው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ከጊዜያዊው ቁሳዊ ዓለም ባሻገር ሌላ ዘለዓለማዊ ዓለም እንዳለ መረጃው ሁሉ በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ቀርቦልናል፡፡ “ፓራስ ታስማት ቱ ብሀቫህ አንያህ” (ብጊ 8.20) ከዚህ ቁሳዊ ዓለም ባሻገር ሌላ ዘለዓለማዊ ወይንም “ሳናታና” ተብሎ የሚታወቅ ዓለም አለ፡፡ እንደዚህም ሁሉ “ጂቫ” ወይንም ነፍስ ዘለዓለማዊ እንደሆነች ተገልጿል፡፡ “ማማይቫምሶ ጂቫ ብሁታ ጂቫ ሎኬ ሳናታናሀ” (ብጊ 15.7) እንደዚሁም ሁሉ ዓብዩ ጌታም “ሳናታና” ወይንም ዘለዓለማዊ እንደሆነ በ11ኛው ምዕራፍ ላይ ተገልጿል፡፡ ስለዚህ ከዓብዩ ጌታ ያለን ዝምድና የቀረበ ስለሆነ በዓይነታችን የተመሳሰልን ሆነን እንገኛለን፡፡ ሶስቱ “የሳናታን ድሀማ ወይንም ዘለዓለማዊው ዓለም” “የሳናታን ወይንም የዘለዓለማዊው ዓብይ ጌታ” እና “ዘለዓለማዊው ነፍሳት” ሶስቱም በአንድ ዓይነት የዘለዓለማዊነት መድረክ ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህም የብሀገቨድ ጊታ ዓላማ ይህንን የሰናታን ወይንም የዘለዓለማዊ መንፈሳዊ አገልግሎቶቻንን ለማነቃቃት ነው፡፡ ይህም ሳናታን ድሀርማ ወይንም የነፍስ ዘለዓለማዊው መንፈሳዊ አገልግሎት ይባላል፡፡ በአሁኑ ግዜ ሁላችንም በተለያዩ ጊዜያዊ እና ቁሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሰማርተን እንገኛለን፡፡ እነዚህም እንቃስቃሴዎች ሁሉ ወደ ንፁህ መንገድ ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ እነዚህንም ቁሳዊ እና ጊዜያዊ እንቅስቃሴዎችን ስናቆም “ሳርቫ ድሀርማ ፓሪትያጃ" (ብጊ 18.66) ዓብዩን ጌታን እንደፍላጐቱ በፍቅር ማገልገል ስንጀምር ይህ ዓይነቱ ሕይወታችን ንፁህና መንፈሳዊ ነው ይባላል፡፡