AM/Prabhupada 0077 - በሳይንቲፊክ እና በፍልስፍና መንገድ ማጥናት ትችላላችሁ፡፡
Ratha-yatra -- San Francisco, June 27, 1971
ክርሽና እንደገለፀውም ሁሉ ትሁት አገልጋዮች በተደጋጋሚ፤ ለሀያ አራት ሰዓት በክርሽና አገልግሎት የተሰማሩ ከሆነ.... ይህም ልክ እንደእነዚህ ተማሪዎች ነው፡፡ ማለትም የክርሽና ንቃተ ማህበር አባሎች ማለት ነው፡፡ እነዚህ አገልጋዮች ለሀያ አራት ሰዓት ያህል በክርሽና የትሁት አገልግሎት ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ማለቴም ይህ ነው የክርሽና ንቃት ትርጉሙ ወይንም የሚያሳደርው ተፅእኖ፡፡ ተማሪዎቹ ሁልግዜ በደስታ እንዳገለገሉ ነው፡፡ ይህም ”የራትሀ ያትራ“ የበዓል ቅንጅት አንዱ ነው፡፡ በዚህም የአንድ ቀን በዓል፤ ሁላችሁም በክርሽና ንቃት ሙሉ በሙሉ ተሰማርታችሁ ትገኛላችሁ፡፡ ይህም ጥሩ ልምምድ ነው፡፡ ይህንንም በመሰለ መንገድ በመላ ሕይወታችሁ የዚህን ዓይነት ልምምድ ብታደርጉ፤ በሕይወተ ህልፈት ግዜ ሽሪ ክርሽናን ለማስተወስ ከቻላችሁ፤ ሕይወታችሁ ስኬታማ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ ዓይነቱ የመንፈሳዊ አገልግሎት ልምምድ ያስፈልገናል፡፡ “ያም ያም ቫፒ ስማራን ሎኬ ትያጃቲ አንቴ ካሌቫራም” (ብጊ፡8 6)]). አንድ ቀን ይህንን ቁሳዊ ገላችንን ትተን መልቀቃችን የማይቀር ነው፡፡ ቢሆንም ግን በዚያች የሕይወተ ህልፈት ግዜ ሽሪ ክርሽናን በፍቅር ለማስታወስ ከቻልን፤ ወዲያውኑ ወደ ሽሪ ክርሽና መንፈሳዊ መኖርያ ለመሸጋገር እንችላለን፡፡ ክርሽና በሁሉም ቦታ ይገኛል፡፡ ቢሆንም ግን ሽሪ ክርሽና በመንፈሳዊው ዓለም የራሱ የሆነ መኖርያም አለው፡፡ ይህም መኖርያ “ጎሎካ ቭርንዳቫን” ይባላል፡፡ እንደምታውቁት የቁሳዊ ገላ ወይንም የዓለማዊ ስሜቶችን አሉን፡፡ ከእነዚህም ስሜቶች በላይ ሀሳባችን ይገኛል፡፡ ይህም ሀሳብ በጣም ረቂቅ የሆነ ነው፡፡ ይህም ሀሳብ እነዚህን ስሜቶቻችንን ሲቆጣጠራቸው ይገኛል። ከዚህ ከሀሳብ በላይ ግን አእምሮ አለ፡፡ ከአእምሮ በላይ ደግሞ ነፍስ ትገኛለች፡፡ ስለእነዚህም መረጃው ላይኖረን ይችላል፡፡ ነገር ግን የብሀክቲ ዮጋን ስርዓት በመከተል የምንለማመድ ከሆነ፤ ቀስ በቀስ ማን እንደሆንን ለመረዳት እንችላለን፡፡ “እኔ ይህ ቁሳዊ ገላ አይደለሁም፡፡” ስለዚህም መረጃ የሌላቸው ታላላቅ መምህራንን እና ታላላቅ ፈላስፋዎችንም ይጨምራል፡፡ እነዚህም ታላላቅ ሰዎች ሁሉ እራሳቸውን እንደ ቁሳዊው ገላ አድርገው በስህተት የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ሁሉም ሰው እንዲህ በማለት ያስባል፡፡ “እኔ ይህ ቁሳዊ ገላ ነኝ፡፡” ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ እኛ ይህ ቁሳዊ ገላ አይደለንም፡፡ እንዳስረዳሁትም.... ቁሳዊው ገላ ማለት የስሜቶቻችን መድረክ ማለት ነው፡፡ እነዚህም ስሜቶቻችን በሀሳባችን ቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው፡፡ ይህም ሀሳብ በአእምሮ ቁጥጥር ስር ያለ ነው፡፡ ይህ አእምሮ ደግሞ በነፍሳችን ቁጥጥር ስር ያለ ነው፡፡ ለዚህም መረጃ አይኖራችሁ ይሆናል፡፡ በመላ ዓለም ስለ ነፍስ መኖር በደንብ የሚያስተምር የትምህርት ቤት ወይንም ስርዓት የለም፡፡ ይህ እውቀት ግን ለሰው ዘር ቀዳማዊ እና በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት ነው፡፡ የሰው ልጅ ሕይወቱን በሙሉ እንደ እንስሶች ማባከን የሚገባው አይደለም፡፡ ይህም በመብላት፣ በመተኛት፣ በወሲብ ግኑኝነት እና በመከላከል ማለት ነው፡፡ ይህም ብቻ ከሆነ የእንስሳ ኑሮ ማለት ነው፡፡ ይህም በተፈጥሮ ተጨማሪ ሆኖ የተሰጠንን ጭንቅላት ወይንም አእምሮ ለዚህ መንፈሳዊ ዓላማ እንድንጠቀምበት ነው፡፡“እኔ ምንድነኝ?” እኔ መንፈሳዊ አካል ወይንም ነፍስ ነኝ፡፡“ ”እኔ መንፈሳዊ አካል ወይንም ነፍስ ነኝ፡፡“ ብለን ከተረዳን፤ ወይንም ደግሞ መረዳት ያለብን ቢኖር፤ ይህ በዓለማዊ አስተሳሰብ የተበረዘ ህይወት በዓለም ውስጥ ብዙ ረብሻን ያመጣ ነው፡፡ በዚህም በቁሳዊ ገላ በተመሰረተ አስተሳሰብ ላይ እያለን እንዲህ ብለን እናሰላስላለን፡፡ ”እኔ ሕንዳዊ ነኝ፡፡“ አንተ ደግሞ ”አሜሪካዊ ነኝ፡፡“ ብለህ ታስባለህ፡፡ ሌላውም ሌላ ያስባል፡፡ ቢሆንም ግን ሁላችንም አንድ ዓይነት ነን፡፡ ሁላችንም መንፈሳዊ አካላት ወይንም ነፍሳት ነን፡፡ ሁላችንም የሽሪ ክርሽና ወይንም የጃጋናት የዘለዓለም አገልጋዮች ነን፡፡
ዛሬ በጣም ደስ የሚልን እና ፀጋ የተሞላበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን ላይ ዓብዩ ጌታ ክርሽና በምድር ላይ በነበረበት ግዜ፤ በሶላር ኤክሊፕስ ግዜ የሚደረገውን የቬዳዎች መንፈሳዊ ስነስርዓት ለመከታተል ወደ ኩሩክሼትራ ተጉዞ ነበር፡፡ ሽሪ ክርሽና የተጓዘውም ከወንድሙ ከባላራም ጋር እና ከእህቱ ከሱባድራ ጋር ነበረ፡፡ መድረሻውም የኩሩክሼትራን ሜዳ ለመጎብኘት ነበር፡፡ ይህም የኩሩክሼትራ ሜዳ በአሁኑም ግዜ በሕንድ አገር ውስጥ ይገኛል፡፡ አንድ ቀን ወደ ሕንድ አገር ብትሄዱም ይህንኑ የኩሩክሼትራ ሜዳ ታገኙታላችሁ፡፡ ይህም የራትሀ ያትራ የበዓል ስነስርአት በየአመቱ የሚደረገው ይህንኑ ለማስታወስ ነው፡፡ ይህም ጌታ ክርሽና ከወንድሙ እና ከእህቱ ጋር የኩሩክሼትራን ሜዳ የጐበኘበትን ግዜ ነው፡፡ ጌታ ጃጋናትንም በማየት ጌታ ቼታንያ መሀፕራብሁ በከፍተኛ ፍንደቃ ላይ ነበረ፡፡ የነበረውም ስሜት ልክ ሽሪማቲ ራድሀራኒ እንደነበራት የፍቅር አንደበት ነበር፡፡ ያስብ የነበረውም እንዲህ እያለ ነበር፡፡ ”ኦ ክርሽና ሆይ እባክህ ወደ ቭርንዳቫን ተመለስ፡፡” በራትሀ ያትራ ሰረገላ ፊት ለፊትም በመደነስ ላይ ይገኝ ነበር፡፡ የታተሙትን መፃህፍቶቻችንን ብታነቡ ይህንን በደንብ ለመረዳት ትችላላችሁ፡፡ እነዚህም መፃህፍት የታተሙት በድርጅታችን ነው፡፡ አንደኛውም መፅሀፍ “የጌታ ቼታንያ ትምህርቶች” የሚል ነው፡፡ ይህም በጣም አስፈላጊ መፅሀፍ ነው፡፡ ስለዚህም የክርሽና ንቃተ ማህበር እንቅስቃሴ በደንብ ለመረዳት ከፈለጋችሁ፤ በድርጅታችን ውስጥ በቂ የሆኑ መፃህፍቶችን አቅርበናል፡፡ ይህንንም በሳይንሳዊ እና በፍልስፍና መንገድ ልታጠኑት ትችላላችሁ፡፡ እነዚህንም መፃህፍቶች ለማጥናት አዝማምያው ከሌላችሁ፤ የሀሬ ክርሽናን ቅዱስ ስም ለመዘመር ትችላላችሁ፡፡ በዚህም መንገድ ሁሉም መንፈሳዊ ሚስጢር ሊከሰትላችሁ ይችላል፡፡ ከሽሪ ክርሽና ጋር ያላችሁንም ግኑኝነት ግልጽ ሆኖ ልትረዱት ትችላላችሁ፡፡ በዚህም የራትሀ ያትራ በዓል እና ስነስርዓት ላይ በመገኘት ስላከበራችሁ በጣም አመሰግናችኋለሁ፡፡ አሁን የሀሬ ክርሽናን ቅዱስ ስም በመዘመር ከጃጋናት ስዋሚ ጋር በመሆን ወደ ፊት መንገዳችንን እንቀጥል፡፡