AM/Prabhupada 1070 - ለዓብዩ ጌታ የፍቅር አገልግሎትን ማቅረብ የነዋሪ ነፍሳት ሁሉ ዘለዓለማዊ ሀይማኖት ነው፡፡

From Vanipedia660219-20 - Lecture BG Introduction - New York

ይህም ”ሰናታን ድሀርማን“ በሚመለከት ደረጃ ሀይማኖት የሚባለውን ቃል ”ድሀርማ“ ከሚባለው የሳንስክሪት ቃል ጋር አጣምረን ለመረዳት ይገባናል፡፡ ይህም ማለት ከአንድ ነገር ጋር ፈፅሞ ሊነጠል የማይችል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ቀድሞ እንደጠቀስነው ስለ እሳት ስናወራ የእሳት ባህርይ የታወቀ እና የተደመደመ ነው፡፡ ይህም ማለት እሳት ሙቀት እና ብርሀንን የሚሰጥ ስለመሆኑ ነው፡፡ ያለ ሙቀት እና ያለ ብርሀን እሳት ብሎ ነገር የለም፡፡ እንደዚህም ሁሉ ከነፍስ ጋር ሁል ግዜ ሊለይ የማይችለው ባህርይ ምን እንደሆነ መርምረን መረዳት ይገባናል፡፡ ይህም ከነፍስ ጋር ተነጥሎ የማይታየው ባህርይ የዘለዓለማዊው የነፍስ ባህርይ ይሆናል፡፡ ይህም ዘለዓለማዊ የነፍስ ባህርይ ዘለዓለማዊው ሀይማኖቱ ነው፡፡ ሳናተን ጎስዋሚ ጌታ ቼይታንያን ስለ ”ስቫሩፕ“ እንዲህ ብሎ ጠየቀው ስለዚህም ስለ እያንዳንዱ ነፍስ ስለአለው ደረጃ ወይንም ”ስቫሩፕ“ ከዚህ ቀደም ተወያይተናል፡፡ ”ስቫሩፕ“ ወይንም ትክክለኛው የነፍሳት ደረጃ ምን እንደሆነ ጌታ ቼይታንያ ተናግሮታል፡፡ ይህም መሰረታዊ የነፍሳት ደረጃ ለዘለዓለም ዓብዩ የመላእክት ጌታን ማገልገል ነው፡፡ ይህንንም የጌታ ቼታንያን ቃል መርምረን ብናጠና እውነትም እያንዳንዱ ነፍሳት በዚሁ በማገልገል ባህርይ በምድር ላይ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡ ይህም አንዱ ፍጥረት ለሌላው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ነው፡፡ እያንዳንዱም ፍጥረት ለሌላው ፍጥረት በተለያየ መንገድ እና ደረጃ አገልግሎቱን ሲያቀርብ ይታያል፡፡ ይህንንም በማድረግ ይኅው ፍጥረት በቁሳዊው ዓለም ውስጥ በመደሰት ይገኛል፡፡ እንስሶች ሰውን ሲያገለግሉ ይገኛሉ፡፡ አገልጋዮችም ጌታቸውን ሲያገለግሉ ይታያሉ፡፡ ሀ ወደ ለ ሂዶ ሲያገለግ ይታያል፡፡ ሐ ደግሞ ወደ መ ሂዶ ሲያገለግል ይታያል፡፡ በዚህም ሁኔታ አንድ ጓደኛም ሌላውን ጓደኛ ሲያገለግል ይታያል፡፡ እናት ልጇን ስታገለግል ትታያለች፡፡ ሚስትም ባሏን ስታገለግል ትታያለች፡፡ ወይንም ባል ሚስቱን ሲያገለግል ይታያል፡፡ ይህንንም መንፈስ እና ምሳሌ ተከትለን ብንመረምር ማንም ሰው ሌላውን ከማገልገል ነፃ የሆነ ሰው ሊገኝ አይችልም፡፡ አገልግሎት የሌለበትን ስፍራ ለማግኘት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ፖለቲከኛውም የእራሱን ማኒፌስቶ ለህዝብ ሲያቀርብ ይታያል፡፡ ለምርጫ የሚያበቁትንም ስለ አገልግሎት መሀላው ሲያሳምናቸው ይታያል፡፡ የፖሎቲካ ሰው መራጮችም የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ የተመኙትን የፖሎቲካ ሰው ይመርጣሉ፡፡ ይህም የተመረጠው ፖሎቲከኛ የሚጠበቅበትን አገልግሎት ለህዝብ ሲያቀርብ ይገኛል፡፡ የንግድ ሱቅ ነጋዴውም ገበያተኛውን ሲያገለግል እንዲሁም ባለሙያተኛው ባለሀብቱን ሲያገለግል ይታያል፡፡ ባለሀብቱም ቤተሰቡን ሲያገለግል እንዲሁም ቤተሰቡም ሁሉ የቤተሰብ ሀላፊውን ሲያገለግሉ ይታያሉ፡፡ በዚህም ዓይነት መንገድ ስናየው ማንም ሰው ቢሆን አገልግሎት ከመስጠት የሚቆጠብ ሊኖር አይችልም፡፡ ይህም አንዱ ፍጡር ሌላውን ፍጡር በማገልገል ላይ የሚታይ ስርዓት ነው፡፡ ከዚህም እንደምንደመድመው አገልግሎት ከማንም ነፍስ ተነጥሎ ሊታይ የማይችል ነገር ነው፡፡ ስለዚህ የነፍስ ሌላውን የማገልገል ባህርይ ዘለዓለማዊው ሀይማኖቱ ነው ለማለት እንችላለን፡፡ አንድ ሰው በአንድ እምነት ውስጥ ገብቻለሁ ብሎ ሲናገር ይህም ከግዜ ከአካባቢው ወይንም ከትውልዱ አንጻር ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም አንድ ሰው እኔ ሂንዱ ነኝ ወይንም እስላም ወይንም ክርስቲያን ነኝ ቡድሀ ነኝ ወይንም ሌላ ሀይማኖት ውስጥ ነኝ ብሎ ሊያምን ይችላል፡፡ እነዚህም የተከፋፈሉ የሀይማኖት ዘርፎች ሳናታን ድሀርማ ናቸው ለማለት አይቻልም፡፡ ሂንዱ የሆነው ሰው እስላም በመሆን ሀይማኖቱን ሊቀይር ይችላል፡፡ ሙስሊም የሆነው ደግሞ ሂንዱ ወይንም ክርስትያን ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እነዚህ የተለያዩ ዓይነት የሀይማኖት እምነቶች የአንድ ሰውን የማገልገል ባህርይ ሊቀይሩት አይችሉም፡፡ ሂንዱም ቢሆን ሙስሊም ወይንም ክርስትያን ሁሉ የሌላ ሰው አገልጋይ ነው፡፡ ስለዚህ የአንድ ሀይማኖት ተከታይ ነኝ ማለት ሳናታን ድሀርማ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ነገር ግን ከነፍስ ተነጥሎ ሊታይ የማይችለው የማገልገል ባህርይ ሰናተን ድሀርማ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ እያንዳንዳችን ዓብዩ ጌታን በማገልገል የዘለዓለም ግኑኝነት አለን፡፡ ዓብዩ የመላእክት ጌታ የበላዩ ተደሳች ነው፡፡ እያንዳንዳችን ነፍሳት ደግሞ የዓብዩ ጌታ ዘለዓለማዊ አገልጋዮች ነን፡፡ እኛ የተፈጠርነውም እርሱን ለማስደሰት ብቻ ነው፡፡ በዚህም በዘለዓለማዊ ደስተኛ የአገልግሎት መስመር ብንሰማራ ደስተኞች እንሆናለን፡፡ ይህም ከዓብዩ ጌታ ጋር በመሆን ነው፡፡ ሌላ ነገር ፍፁም የሆነ ደስታ ሊሰጠን አይችልም፡፡ በተገነጠለ መንገድ ወይንም ቀደሞ እንደተገለፀው በገለልተኝነት መንገድ ደስተኞች ልንሆን አንችልም፡፡ ማናቸውም የገላችን ክፍልም ቢሆን ይህም እጃችን፣ እግራችን፣ ጣቶቻችን፣ ወይንም ማናቸውም የገላችን አካል ከሆዳችን ጋር ሳይተባበሩ በገለልተኝነት መንገድ በመስራት ደስተኛ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ነፍሳት በገለልተኝነት ከዓብዩ ጌታ አገልግሎት ውጪ ደስተኛ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ይህም ማለት ለዓብዩ የመላእክት ጌታ መንፈሳዊ አገልግሎትን ካላቀረቡ ደስተኛ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ለምሳሌ በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ የተለያዩ አምላኮችን ማምለክ የተደገፈ አይደለም፡፡ ይህም በብሀገቨድ ጊታ በሰባተኛው ምዕራፍ እና በሀያኛው ጥቅስ ውስጥ ተገልጿል፡፡ ዓብዩ ጌታም እንዲህ ተናግሯል ”ካሜይስ ቴይስ ግያና ፕራፓድያንቴ ንያ ዴቫታሀ“ ”ካሜይስ ቴይስ ቴይር ህርታ ግያናህ“ እነዚያ በስግብግብነት የተገፋፉ ሁሉ መላእክትን ብቻ እንጂ ዓብዩን የመላእክት ጌታ ሽሪ ክርሽናን አያመልኩም፡፡